Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ስሎቬኒያ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ ሪፐብሊክ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የስሎቬኒያን ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርክ ሙሳር በብሔራዊ ቤተመንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።

ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ በዓለም አቀፍና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በመምከር በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ስፔስ ሳይንስና ሌሎች ዘርፎች በትብብር ስለሚሰራበት ሁኔታ መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርክ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር በምጣኔ ሃብት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የውሃ አስተዳደርና ሌሎች ዘርፎች በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ አንስተዋል፡፡

ዛሬ ጠዋት የዓድዋ ድል መታሰቢያን በመጎብኘት የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡት ፕሬዚዳንቷ፤ በተመሳሳይ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ጉብኝት ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ ፕሬዚዳንቷ ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ህፃናትን የሙያና ሥነ ምግባር ሥልጠና በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉና ከቤተሰባቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እያደረገ የሚገኘውን የቦስኮ ልጆች ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በጉብኝታቸው በስሎቪኒያ ሕዝብና መንግስት ድጋፍ የሚተገበረውን ዘመናዊ የንብ ማነቢያ ሠርቶ ማሳያና የስልጠና መስጫ መርሐ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።

መርሐ ግብሩ በንብ ማነብ ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያግዝ በመሆኑ ስሎቬኒያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.