ደስታ ሙሉ የሚሆነው ሌሎችን መርዳት ሲቻል ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዒድ አል ዓድሃ በዓል በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ሐይማኖታዊ ትዕዛዛትን በማከናወን ይከበራል፡፡
በዓሉ ዒድ አል አድሃ ወይም የዕርድ ቀን (በዓረብኛ የሙን ነኽር) ተብሎ እንደሚጠራ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ መስጂዶች የእስልምና መምህር የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ጣሃ ይናገራሉ፡፡
በሂጅራ አቆጣጠር የመጨረሻው ወር የሆነው ዙል ሂጃህ በገባ በዘጠነኛው ቀን አረፋ እንደሚውል እና ዒድ ዓል አድሃ ደግሞ በማግስቱ ወይም በ10ኛዋ ቀን እንደሚከበር ያስረዳሉ፡፡
በዕለቱ የሀጅ ተጓዦች በአረፋ ተራራ ወይም ሜዳ ላይ በመሆን ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ አላህን ይማፀናሉ፤ እዝነቱን ይከጅላሉ፡፡
የአረፋ ተራራን መውጣት ለሁጃጆች ልዩ ትርጉም አለው የሚሉት ኡስታዝ ካሚል፤ የሀጅ ተጓዦች የምኅረት፣ ይቅርታና ጸጸት እንዲሁም መስዋዕትነት ማሳያ በሆነው ቀን ተራራውን መውጣት ከአላህ ጋር የመቀራረብ ዕድል ይሰጣል ይላሉ፡፡
ዒድ ዓል ዓድሃ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትዕዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎ እንደሚከበርም ይናገራሉ፡፡
እንዲሁም አረፋ አዳምና ሄዋን ከገነት ወጥተው ለረጅም ዘመናት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ በአረፋ ተራራ ላይ መገናኘታቸው የሚዘከርበት በዓል መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የዒድ ዓል ዓድሃ በዓልን ሲያከብር ሐይማኖታዊ ትዕዛዛትን በመከወን ሊሆን እንደሚገባም መክረዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የዕርድ ሥነ-ሥርዓት መከናወን ያለበት ጠዋት ከሚሰገደው የዒድ ሰላት በኋላ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በዚህ ለምግብ ፍጆታ የሚሰናዳው ዕርድ ለሦስት እንደሚከፈል እና፤ አንዱ ለተቸገሩ ወገኖች፤ ሁለተኛው ወደ ቤት ለጥየቃ የሚመጡ ወዳጅ ዘመዶች የሚስተናገዱበት እንዲሁም ሦሥተኛው ለራስ የሚቀመጥ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ደስታ ሙሉ የሚሆነው የተቸገሩ ወገኖችን መጠየቅ ሲቻል መሆኑን በመገንዘብ፤ በዚህ አግባብ ዒድ ዓል ዓድሃን ማክበር ይገባል ብለዋል፡፡
በዓሉ፤ የአላህን ትዕዛዛት የምንፈጽምበት እና የደስታ ይሁን ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በነገው ዕለት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ይከበራል፡፡
በዮሐንስ ደርበው