Fana: At a Speed of Life!

የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ዓመት ያላነሰ ጊዜ በተከታታይነት እያደገ መጥቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ዓመት ያላነሰ ጊዜ በተከታታይነት እያደገ መጥቷል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት፣ ወቅታዊ ፈተናዎች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ባደረጉት ሁለተኛው ክፍል ልዩ ቃለ መጠይቅ ላይ ነው ይህንን የገለጹት።

በዚህም በለውጡ ማግስት በሀገሪቱ ለዓመታት ሲጓተት የመጣውን የዋጋ ግሽበት ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁም የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መከሰቱ ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሀገራት ለራሳቸው ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ይህም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ የሚያግዙ የተለያዩ ሀገራት እርዳታቸውን፣ ትብብርና እንዲሁም ድጋፋቸውን በማስተጓጎል የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር አስተዋጽዖ ማድረጉን አብራርተዋል።

በዚህም ምክንያት ወደ አፍሪካ ሀገራት የሚፈሰው ድጋፍ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰና ይህም ከነበረው ችግር በመደገፍ ለመውጣት ፈተና እንደነበር አመልክተዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶች ሙሉው አቅሙን በኢኮኖሚ ላይ እንዳናውል ጊዜውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን መውሰዱ ተጨማሪ ችግር ሆኖ መጥቷል ብለዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ በኋላ የዋጋ ግሽበት ለሁሉም ሀገራት ፈተና ሆኖ መምጣቱን አንስተው÷ ከውጪ በሚገቡ እቃዎች ጭምር የዋጋ ግሽበት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ እንደነበር ገልጸዋል።

ይህንንም ችግር በምዕራፍ በመከፋፈል ለመፍታት በትኩረት መሰራቱን አስረድተው÷ በመጀመሪያው ምዕራፍ በማፍታታት አቧራውን ለማራገፍና እሴት ለመጨመር የመሞከር ሥራዎች መሰራቱን ተናግረዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ማንሰራራት እንዳለብን በመግባባት ቀስ ያለው አካሄድ ከነበርንበት ችግር እንደማያወጣ በመገንዘብ÷ ተቋማትን በመገንባት እንፍጠን፤ እንፍጠር በሚል ውሳኔዎችን በማሳለፍ የተለያዩ ስራዎች መሰራቱን አስታውሰዋል።

ባላፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ በአማካይ የኢትዮጵያ መንግስት ለደመወዝ የሚያወጣው ገንዘብ በየዓመቱ 21 በመቶ እንደሚጨምር አንስተው÷ ይህም ወጪ ለእያንዳንዱ ሰራተኛ እንደማይደርስ አመላክተዋል።

የመንግስት ሰራተኛ ከለውጡ በፊት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን አካባቢ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ አሁን ላይ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የመንግስት ሰራተኛው ቁጥር 44 በመቶ መጨመሩንና ከዚህም ውስጥ ከለውጡ በፊት የነበረው የመምህራን ቁጥር 36 በመቶ መጨመሩንና ባለው መጠን ብቻ የመምህራንን ደመወዝ 36 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል።

ይህም የነበረውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የተወሰደው ርምጃ እንደሆነና ከ35 ሺህ በላይ መዋለ ህፃናት በኢትዮጵያ ውስጥ መገንባቱን ተናግረዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.