Fana: At a Speed of Life!

እየመጣ ያለውን ለውጥ በተገለጠ ዓይን ማየት፣ መጠበቅና መደገፍ ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እየመጣ ያለውን ለውጥ በተገለጠ ዓይን ማየት፣ መጠበቅና መደገፍ ያስፈልጋል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት፣ ወቅታዊ ፈተናዎች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ባደረጉት ልዩ ቃለ መጠይቅ በሀገሪቱ ያሉ የህክምና መስጫ ጣቢዎች የማስፋት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት የጤና ባለሙያ 53 በመቶ መጨመሩን ጠቅሰው፥ ይህ ሥራ ባይሰራ ኖሮ የጤና ተቋማት በሀገሪቱ አሁን ያለውን ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

በዚህም በህክምና ሙያ ላይ የሚሰራው የህክምና ባለሙያ ቀጥታ ደመወዝ አገኘ ወይ ቢባል ላያገኝ ይችላል ግን በቀን 50 ሰው የሚያይ ከነበረ በተወሰነ ደረጃ በየቦታው የሚያግዝ ሰው ሲፈጠር ያ ቁጥር ይቀንሳል ብለዋል።

ይህም ሌላ ሁለተኛ ሰው የሥራ ዕድል እንዲያገኝና ቀድሞ የነበረው ባለሙያም ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን አንስተው÷ ይህ በቁጥር ያለው ዕድገት እንደሆነ አመላክተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ዓመት 91 ቢሊየን ብር የደመወዝ ጭማሪ መደረጉን ገልጸው÷ ዝቅተኛውን ተከፋይ ደመወዝን በማሳደግ የኑሮ ጫናን እንዲቋቋሙ ለማድረግ ተሰርቷል ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ያላት አቅሟ እንደሆነና ከዚህ በላይ እንደማትችልና የተደረገውንም አምጣና ብዙ ነገር ቀናንሳ ማድረጓን ገልጸው÷ ከዛ በላይ ቢጨመር ጠቃሚ እንደሆነና የመንግስት ሠራተኛው ደመወዝ በቂ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በአንድ በኩል ስብራት እንጠግናለን በሌላ በኩል ሀገር እንሰራለን ስላልን በተወሰነ መንገድ መስዋዕት ካልከፈልን የምናስበውን ነገር ማሳካት አንችልም ብለዋል።

ዘንድሮ የፌዴራል መንግሥት ለሰራተኛ ደመወዝ የሚከፍለው ከሚገባው ገቢ ግማሽ ያህሉን እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተወሳሰበ ችግርና የተከማቸ በሽታ ውስጥ ያለ ሀገር በአንድ ጊዜ ያንን ሰብሮ መውጣት ስለሚያስቸግር መሰረት የሚጥሉ ሥራዎችን እየሰራን በሂደት በየደረጃ እየፈታን መሄድ ይጠይቃል ብለዋል።

ኑሮ ውድነትን ማስተካከልና ዕድገትን አብሮ ማምጣት አውሮፕላን እየበረረ መጠገን ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማቆም ቢቻል ለጊዜው ግሽበት እንደሚቆምና አገርሽቶ ሊመጣ እንደሚችል አመልክተዋል።

እያደግን ነው ግሽበትን ለመግራት እየሰራን ያለነው ሲሉም አክለዋል።

ካሰብነው በላይ ለውጥ እየመጣ ነው በማለት ገልጸው÷ ይህንንም በተገለጠ ዓይን ማየት፣ መጠበቅና መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.