የስሎቬኒያ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀቁ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የስሎቬኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር በኢትዮጵያ የነበራቸውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቅቀው ወደሀገራቸው ተመለሱ፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላ ማረፊያ ተገኝተው ሽኝት አድርገውላቸዋል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጋር የሀገራቱን የዲፕሎማሲ ትብብር በማጠናከር በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ዘርፎች ላይ መክረዋል፡፡
ከፕሬዚዳንት ታዬ ጋር በብሔራዊ ቤተ-መንግስት በነበራቸው ውይይት፤ ኢትዮጵያና ስሎቬኒያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በኅዋ ሳይንስ በትብብር ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
ፕሬዚዳንቷ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን ዘመናዊ የንብ ማነብ ሰርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ የነበራቸው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው መገለጹን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡