Fana: At a Speed of Life!

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል የህብረተሰቡ ሚና ..

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥላቻ ንግግር፣ ሀሰተኛ መረጃዎችና ነጠላ ትርክት የህብረ ብሔራዊ አንድነት ፈተናዎች ናቸው፡፡

ለፋና ዲጂታል ሙያዊ ሀሳባቸውን ያጋሩ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ምሁራን እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ የህብረተሰቡን የሚዲያ ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ምሁራኑ እንደሚሉት፤ በተለይም የዲጂታል ሚዲያው ካመጣቸው መልካም ዕድሎች በተቃራኒ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ እንዲስፋፋ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያው የሚሰራጩበት አንዱ ምክንያት መልዕክቶቹ በህብረተሰቡ ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳቶች አስቀድሞ ባለመረዳት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ኤሊያስ ወርቁ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ሆን ብለው ሰዎችን ለማሳሳትና ለማጋጨት መሰል መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የዲጂታል ሚዲያውን በእውቀት፣ በአስተውሎትና በኃላፊነት መጠቀም ከተቻለ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡

ነገር ግን የተገኘውን እድል ለበጎ ዓላማ ከመጠቀም ይልቅ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ለጥፋት በሚጠቀሙ ሰዎች ምክንያት ዲጂታል ሚዲያው የስጋት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ፡፡

የህብረ ብሔራዊ አንድነት ፈተና የሆኑትን የጥላቻ ንግግር፣ ሀሰተኛ መረጃዎችና ነጠላ ትርክትን ለመከላከል ከመንግስት እርምጃዎች ባሻገር የህብረተሰቡ ሚና ወሳኝ መሆኑን ነው ምሁራኑ የሚገልጹት፡፡

መንግስት የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቆጣጠር ህግ በማውጣት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በህግ ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ ህብረተሰቡ የሚደርሱትን መረጃዎች በሙሉ እውነት ነው ብሎ ከመቀበል ይልቅ በጥንቃቄ ሊመረምር እንደሚገባ ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር) ይመክራሉ፡፡

ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክሩት ኤሊያስ ወርቁ (ዶ/ር) ህብረተሰቡ እውነተኛና ሀሰተኛ መረጃዎችን መለየት የሚችልበትን መሰረታዊ ግንዛቤ መፍጠር ከመንግስት፣ ከሚዲያዎችና ከዘርፉ ምሁራን እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡

በተመሳሳይ በማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ተከታይ ያሏቸው የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃንና ሌሎችም አካላት መረጃዎችን ሲያሰራጩና መልዕክት ሲያስተላልፉ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ ሊሆን እንደሚገባ ምሁራኑ አመላክተዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.