Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ሰፊ የሆነውን የቆላ መሬት አበክረን መጠቀም አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጀመረውን እና አበረታች ውጤት እያሳየ ያለውን የቆላማ አካባቢ ልማት በይበልጥ በማጠናከር አበክረን መሥራት አለብን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ባለ አራት ክፍል ቃለ ምልልስ በክፍል ሦስት ከቆላ ልማት ጋር ኢትዮጵያ እያከናወነች ስላለው እና በቀጣይ ስለሚሠሩ ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም አንዱ የዕይታ ለውጥ ያመጣንበት መንገድ ከጫፍ እስከ ጫፍ የኢትዮጵያን መሬት፣ ሰው እና ዕውቅት መጠቀም አለብን የሚለው ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም መደመር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ያልተደመረ አቅም፣ ዕውቀት እና ሀብት የምናስበውን ብልጽግና አያረጋግጥም ነው ያሉት፡፡

ቆላ ችግር አይደለም፤ ለቆላ አካባቢዎች ያለን ዕይታ መቀየር አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባይታይ ነው እንጂ ቆላ ውስጥ ሀብት አለ፤ ቆላ ውስጥ ለኢትዮጵያ ብልጽግና አጋዥ የሆኑ ጉልበቶች አሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ቆላማ አካባቢዎች ባላቸው ጸጋ ልክ መሬቱን፣ ውኃውን እና ሰውን እየደመርን በሚፈለገው ልክ ለልማት ማዋል ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የቆላ ሀብት ሀገሪቱን የማልማት አቅም እንዳለው ገልጸው፤ ለምሳሌ የደቡብ ኦሞን የተፈጥሮ ጸጋ በማንሳት በዚህ አካባቢ ከፍተኛ የውኃ አቅም ያለው 145 ኪሎ ሜትር መስኖ መሠራቱን አስረድተዋል፡፡

ይህን በአግባቡ ማሽን በመጠቀም አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሀገር በምግብ እራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሶማሌ፤ አፋር እና ቦረናም እንደዚህ አይነት ከፍተኛ አቅም መኖሩን አመላክተዋል፡፡

ቆላ በኢትዮጵያ ሰፊ ነው፤ ቆላ ማለት በቀላሉ በማሽን ለማልማት የሚመች መሬት መሆኑን አስገንዝበው፤ መሬቱን ብቻ ሳይሆን ሰውን ደምረነዋል፤ ቀደም ሲል የነበረው አጋር የሚባል የለም፤ ሁሉም እኩል እንዲታይ አድርገናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ ስንዴ አምራች መሆኗን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንደኝነት ብቻ ሳይሆን በአህጉሪቱ ሁለተኛ አምራች የሆነችውን ግብጽን በሦስት እጥፍ ትበልጣለች ነው ያሉት፡፡

ይህን ለማራከስ መጣር ትክክል እንዳልሆነም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘም፤ ምን ያህል መሬት እንደታረሰ መዞር አይጠበቅብንም፤ ባለንበት ሆነን ማወቅ የሚያስችል የሳተላይት መረጃዎችን እንመለከታለን ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡

ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ስንዴ ከውጭ አላስገናባንም፤ ከዚያ በፊት እስከ 1 ቢሊየን ዶላር እናወጣ ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

መታወቅ ያለበት ግን ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን እያስተናገደች ያለች ሀገር በመሆኗ ዓለም አቀፍ ተቋማት ስንዴ እያስገቡ ሊረዱ ይችላሉ፤ ይህ ማለት ለኢትዮጵያ ረዱ ማለት አይደለም፤ ከተለያዩ ሀገር መጥተው ለተጠለሉ ስደተኞች እንጂ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቅርቦትና ሸማችን በማገናኘት ረገድ በርካታ ፈተናዎች አሉ፤ ማምረት ስለቻልን ብቻ ስኬታማ ነን ማለት አይደለም፡፡ በቀጣይ ልንተገብራቸው የሚገቡ በርካታ ተግባራት እንዳሉ እናውቃለን ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ቆላ ላይ አበክረን መሥራት ይጠበቅብናል፤ አጋር ነህ መሬቱ የኛ ነው ማለት አይቻልም፤ ሰውም መሬቱም የጋራ ነው፡፡ ተባብረን እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.