ኢትዮጵያ ገዝፋና ጸንታ ለልጆቻችን ማሸጋገር እንድንችል አብሮነትን ታሳቢ ያደረገ ትርክት መከተል ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ገዝፋ አና ጸንታ ለልጆቻችን ማሸጋገር እንድንችል ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ እና የጋራ አብሮነትን ታሳቢ ያደረገ የትርክት ስርዓት መከተል ያስፈልጋል አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በክፍል ሦስት፤ የትርክት ግንባታ ላይ ትኩረት መስጠት ለምን እንዳስፈለገ አብራርተዋል።
በማብራሪያቸውም ሰዎች ትርክት ችግር መሆኑን የሚገነዘቡት በብሔር በሃይማኖት ስለምንጨቃጨቅ ከፋፋይ ነገር ስለተነገረን በሚል ብቻ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ትርክት በየቀኑ ለልጆቻችን እና ለራሳችን የምንነግረው ነው ብለዋል።
በትምህርት ቤት የማትችል፣ የማታውቅ፣ የማይሳካልህ፣ ሰነፍ ወይም ከእነእገሌ የምታንስ የሚሉ ትርክቶች በየቀኑ የሚሰሙ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸው፤ በአሸናፊና ተሸናፊ ስነ ልቦና የተሞላው የየዕለት ውሏችን የትርክት ውጤት ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
መምህራንና ጓደኞች የሚፈጥሩት አሉታዊ አገላለጽ የሰውን ውስጣዊ ስነ ልቦና እየሰበረው ስለሚሄድ መጨረሻ ላይ ሙሉዕነት ያለው ዕሳቤ ማሰብ እንደሚቸግር አስገንዝበዋል።
እንደዚህ ያሉ ቅስም ሰባሪ እና ህልውና አዋኪ ንግግሮች ተሰናስለው አደገኛ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ በተቋም፣ በተደራጀ ሃይል ደግሞ ሲሆን ውስጥን እያደቀቁ ይሄዳሉ ብለዋል።
የእሱ ዘር አይረባም ያንተ እምነት እንደዚህ ነው ያንተ ትምህርት እንደዚህ ነው የእሱ አይረባም የሚባለው ቋንቋ በጥፊ፣ በቦክስ፣ በጥይት እንደመምታት ስለማይታይ ነው እንጂ ውስጣችንን እያደቀቀ የሚሄድ ነገር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በብሔሩ ባያስብ በራሱ የማይተማመን በርካታ ሰው ፈጥሯል፤ በሃይማኖቱ ባይመካ እና በሃይማኖቱ ሰው ባይሳደብ በራሱ ምሉዕነት የማይተማመን እና ከማድረግ ይልቅ በመታዘብ የሚያሳልፍ ብዙ ሰው ፈጥሯል ብለዋል።
ስብራቱ በጣም ሰፊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በትምህርት ስርዓቱ፣ በሚዲያው፣ በዕምነት ተቋማት ስብከት መታየት አለበት በእያንዳንዱ ላይ በሚዘራው ስብከት እራሱ ሃይል የሚሰጥ ነው ወይስ ያንን የሚያሳጣ ነው የሚለው መታየት አለበት በማለት አብራርተዋል።
የቤተሰብ ወሬ፣ የጓደኞች ድርጊት ሁሉ መታየት እንዳለበት ገልጸው፤ እነዚህ ሁሉ ተሰናስለው ነው እንደ ሀገር ያለንን የተስተካከለ ትርክት የሚፈጥሩት ብለዋል።
ግለሰብና ማህበረሰብ የሚሰራበት መሰረታዊው የሥሪት ምሰሶ ትርክት ነው በማለት ጠቅሰው፤ ሰዎች ደሃ ናችሁ፣ ያደጋችሁ የበለጸጋችሁ ናችሁ እንዲሁም ሰላም ግጭት ትርክት ነው በማለት አስረድተዋል።
ለአብነትም አበዳሪዎች አናበድርም የሚሉት ግጭት አለባችሁ፤ ደሃ ናችሁ አትከፍሉም ነው እንጂ የኢትዮጵያ ዕዳ ከአፍሪካ አንደኛ፣ ሁለተኛ ሶስተኛ እየተባሉ ከሚደረደሩ ሀገራት በንጽጽር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
ያለባቸው ዕዳ እኛ ካለብን ዕዳ በብዙ እጥፍ ይበልጣል ያ ዕዳ ወደ እኛ ዕዳ ልክ ቢገባ ምናልባት እኛ በብዙ እጥፍ እንበልጣቸዋለን ነው ያሉት።
ለጋራ ግብ የሚቆም ትውልድ ላይ አይተኬ ሚና የሚጫወተው ትርክት ሁሉንም ዘውግ የሚነካ እንደሆነ ገልጸው፤ ፊልሞቻችን፣ ሙዚቃዎቻችን ብዙ ነገራችን መፈተሽ አለበት ብለዋል።
ያለንን፣ የታጠቅነውን እና የምናውቀውን እውነት የሚያስጥል የድግግሞሽ ውሸት ሲፈጠር የእኛን ቁመና፣ አቋም፣ ቦታ እና ሁኔታ ይቀይረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ትርክት ግለሰብንና ማህበረሰብን ሊጎዳ የሚችል አደገኛ ነገር በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ሲሉ አስረድተዋል።
በተለይ ዘር፣ ሀይማኖት እየተባለ በሚነገርበት ሀገር ውስጥ እንደዚህ አይነት ከፋፋይ ጉዳይ ካለ ጥፋት ያመጣል፤ ሊገራ ሊታረም ይገባዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ንቅል ልሂቃን ከፋፋይ የሆነ ትርክት እያሰረጹ ትውልድ በትውልድ ላይ፤ ሰው በሰው ላይ ዜጋ በዜጋ ላይ ተባብሮ ልማትን ብልጽግናን እንዳያመጣ እርስ በርስ እንዲጠራጠር እንዲጠፋፋ መንገድ እየከፈቱ ነው ብለዋል።
እነሱ የዜሮ ድምር ጨዋታቸውን በህዝብ ላይ ሲያደርጉት ያንን የሚገዛ ሰው ደግሞ እየተበራከተ ሲሄድ እርስ በርሳችን ሊያጠፋፋን ስለሚችል ልጆቻችን ላይ ከታች ጀምሮ ልንሰራባቸው ይገባል በማለት አስገንዝበዋል።
ሚዲያዎቻችን ድራማዎቻችን ፊልሞቻችን ፕሮጀክት የሚያደርጉት መሰብሰብን አንድነትን አብሮነትን መሆን አለበት በማለት ገልጸው፤ በየሰፈሩ ኳስ ሜዳ፣ አምፊና ፓርኮች የሚሰሩት ሰብሰብ ብለው እንደ ጓደኛ የሚተያዩበት ባህል እየጠፋ ስለሆነ ይህን ለመጠበቅ እንደሆነ አመላክተዋል።
እነዚህ ሁሉ ሰው ከቋንቋ፣ ከእምነት፣ ከጾታ፣ ከተወለደበት ሰፈር ባሻገር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር አብሮ ገብቶ ወጥቶ ደስታንና መልካም ዕውቀትን ሊጋራ የሚችል አውድ መፍጠር አስፈላጊ ስለሆነ ነው ብለዋል።
ሚዲያዎቻችንም ከዛ አንጻር ከተገሩ ሰዎቻችንም ከነቁ፣ ትርክት እየተገራ ከሄደ በብዙ ሀገራት እንደምናየው የተሰበሰበ ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል በማለት ገልጸው፤ ብዙ ሀገራት የፖለቲካ፣ የብሔር፣ የቋንቋ እና የእምነት ልዩነት ቢኖርባቸውም በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ግን ሲያወላዱ እንደማይታዩ ተናግረዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ግን አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ የሁሉ ነገር ትኩረት መነሻና መዳረሻ በመሆኑ ይህንን ለመግራት የሚሰበስብ፣ የሚያስማማ እና የሚያቀራርብ፣ ከልመና ከድህነት የሚያወጣ እንዲሁም ተቋም ለመገንባት እና በጋራ ለመኖር የሚያስችል አውድ የሚፈጥር ትርክት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ትርክት የተሳሳተ መረጃ የተሳሳተ ወሬ ሆኖ ከሚከፋፍለን መልካሙን ነገር ዘርተን መልካም ትውልድ መፍጠር አለብን የሚል እሳቤ ነው ያለው በማለት ጠቅሰው፤ ትርክት ካልተገነባ በቀር ሉዓላዊነቷ የተከበረ የገዘፈች ኢትዮጵያን መፍጠር እንደማይቻል አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ገዝፋ ጸንታ ለልጆቻችን ማሸጋገር እንድንችል ቀናነት ያለበት ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ የጋራ አብሮነትን ታሳቢ ያደረገ ልዩነታችንን ያልደፈጠጠ የትርክት ስርዓት መከተል ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል።
ይህንን በማድረግ ነው የተሟላ ብልጽግና ልናረጋግጥ የምንችለው በሚል እሳቤ ነው ትርክት ላይ አበክረን የምንሰራው ብለዋል።