Fana: At a Speed of Life!

23 ሚሊየን ሰው ከተረጂነት ነጻ መውጣቱ የኢትዮጵያ ማንሠራራት ማሳያ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ባለ አራት ክፍል ቃለ ምልልስ በክፍል ሦስት፤ ኢትዮጵያ ተረጂነትን የምትጸየፍ እና ይህን ለመቅረፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ዐበይት ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም፤ ተረጂነት በተለይ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በጣም አሳፋሪው ነገር ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሚያህል ሀገር ለራሷ አምርታ ማብላት ተስኗት፤ አንዳንድ ጊዜም ከእሷ ከሚያንሱ ሀገራት መለመኗ አሳፋሪ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ ትውልድ ጨክኖ ከዚህ አሳፋሪ ነገር ኢትዮጵያን መገላገል አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ልጆቻችን ግን ይህን ጉዳይ ከታሪክ ውጭ በተግባር ሊያዩት አይገባም ነው ያሉት፡፡

እኛ ተረድተን፤ ተረጂነትን ማውረስ የለብንም፤ እኛ ለምነን ልመናን ማሸጋገር የለብንም፤ እኛ ጋ መቆም አለበት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ካጋጠመን የሥነ-ልቦና ሥብራት አንዱ ከተረጂነት ጋር የሚያያዝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሳፋሪ የሆነው ተረጂነት፤ ጌጥ እና ክብር መሆን የለበትም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደሀገር እምነት (እሴት) መሸርሸር አስፈሪ ነው፤ ለምሳሌ በሴፍቲኔት ለመታቀፍ ሲሉ ጥሪታቸውን የሚሸጡ መኖራቸውን በጥናት አረጋግጠናል፤ ድሃ ለመባል ያሏቸውን እንስሳት እንደሚሸጡ ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡

ባለኝ ላይ ጨምሬ ከልመና ልገላገል ሳይሆን፤ ምንም የለኝም ድሃ ነኝ በሴፍቲነቴት ልታቀፍ የሚሉ አሉ፤ ይህ የሥነ-ልቦና ሥብራት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ ልጅ እየቀያየሩ የሚለምኑም አሉ ነው ያሉት፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ከታች ያሉ አመራሮችም ከዚህ ጋር በተያያዘ መሸማቀቅ የሌላቸው ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች አሉ ነው ያሉት፡፡

በአንጻሩ ተረጂነትን የሚጸየፉ እና ከዚህ ለመውጣት በትብብር እንድንሠራ የሚያነሳሱ መኖራቸውን በተለያዩ የውይይት መድረኮች ዐይተናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዕርዳታን ለማቆም በመንግሥት የተደራጀ ቢሮ መኖሩን ጠቁመው፤ በአጠረ ጊዜ ዕርዳታን ለማቆም በአግባቡ እየሠራን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ 27 ሚሊየን ገደማ ተረጂ እንደነበራት አውስተው፤ በዚህ ዓመት ያለው የተረጂ ቁጥር 3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህ በሠራነው የተለያየ ሥራ 23 ሚሊየኑ ነጻ መውጣቱን ያሳያል፤ ይህ ትልቅ ድልም ነው፤ የኢትዮጵያ ማንሠራራት ማሳያም ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

ከ3 ነጥብ 9 ተረጂዎች ከ1 ሚሊየን በላይ ያህሉ በውስጥ ግጭቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ናቸው፤ በፍጥነት ወደመኖሪያቸው ሲመለሱ የተረጂ ቁጥር በአጭር ጊዜ ይቀንሳል ብለዋል፡፡

መንግሥት ባስቀመጠው ዕቅድ እና ሕዝባችን በነበረው መንገድ ድጋፉን አጠናክሮ ከቀጠለ የኢትዮጵያ እና የዕርዳታ ጉዳይ ቢበዛ ሁለት ዓመት ነው፤ ከዚያ በላይ አይቀጥልም ሲሉ አመላክተዋል፡፡

ይህን ስኬት ለማምጣት የተሄደበትን መንገድ ሲያብራሩም፤ የተስማማ ተፈጥሮ መኖርና በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት መቻል፤ የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ የተለያዩ ኢኒሺቲቮች ትግበራና ስኬታማነት፣ ቆላን ጨምሮ የበጋ እርሻን በአግባቡ ለመጠቀም የተደረጉ ጥረቶች እና መረጃ (ዳታ) የማጥራት ሥራን ጠቅሰዋል፡፡

የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ከእያንዳንዱ ትራንዛክሽን ፈንድ ማሰባሰብ፣ ሳይበላሽ የሚቆይ በቂ የእህል ክምችት እንዲኖር ማስቻል፣ የዕርዳታ ኮሚሽን እርሻ ላይ በስፋት እንዲሠራ ማድረግ፣ የመንግሥትን ለአደጋ ምላሽ የመስጠት አቅም ማጎልበት፣ ማዕድ ማጋራትን እና የትምህርት ቤት ምገባን ማስፋፋት የሚሉትን ዘርዝረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያንሠራራች ነው፤ በቀጣይ ዕርዳታን በማቆም ወደ አጋዥነት መሸጋገር አለባት፡፡ በጥቂት ዓመታት ተረጂ የነበረን 23 ሚሊየን ወገን ነጻ ማውጣት ቀላል አይደለም፤ በተገኘው ውጤት እንኮራለን፤ በቀጣይ ብዙ እንድንሠራም አቅም ይሆነናል ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.