የኢኮኖሚ ማሻሻያው በቂ ዝግጅት ተደርጎ በመተግበሩ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል – አቶ አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በቂ ዝግጅት ተደርጎ በመተግበሩ በሁሉም ዘርፎች ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል አሉ፡፡
ሚኒስትሩ ወቅታዊ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ጉዳዮችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ÷ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ በሚያስችል አበረታች ሒደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲተመን መደረጉ፣ የፊስካል ፖሊሲና አዲስ የገንዘብ ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረጋቸው እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች መከናወናቸው ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የምንዛሪ ግብይቱ በተረጋጋ መልኩ እንደቀጠለ እና በከፍተኛ ሁኔታ ያደገበት ዓመት መሆኑን ጠቁመው÷ የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉም የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመላከቱት ሚኒስትሩ÷ከፍተኛ የገቢ ዕድገት እንዲመዘገብ እና የዋጋ ግሽበት ዝቅ እንዲል ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ሁሉም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ- ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የሌሎችም አፈጻጸም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግም በኢኮኖሚው የሚደርጉት አስተዋጽኦ ይበልጥ እንዲጎለብት መከታተል ብሎም ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ አመርቂ ሥራዎችን እየከወነ ነው ብለዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት መንግስት ከፍተኛ የበጀት ድጎማ ማድረጉን ጠቅሰው÷ይህም የውጭ ምንዛሪ ተመኑ በገበያ በመወሰኑ ምክንያት ሊፈጠር የነበረውን ጫና መቋቋም ማስቻሉን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከ10 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ለሚገኘው የከተማና ገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ወደ 60 ቢሊየን ብር በመመደብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡