አዲስ አበባ ሕግና ሥርዓት የሰፈነባት ከተማ እንድትሆን የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ ሕግና ሥርዓት የሰፈነባት ከተማ እንድትሆን የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል አሉ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በስድስተኛ ዙር 2 ሺህ 74 ፓራ ሚሊተሪ ኦፊሰሮችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ መዲናዋን ለነዋሪዎች ምቹና ተስማሚ ለማድረግ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራዎች በሕግና ሥርዓት እንዲመሩ የደንብ ማስከበር ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
በዚህም አዲስ አበባን ሕግና ሥርዓት የሰፈነባት ፤ ሁሉም አሰራር በሕግ እና ደንብ የሚመራባት ከተማ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የዕለቱ ተመራቂዎች በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት እና ክህሎት ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
ደንብ አስከባሪዎች ሕዝብን አክብረው ደንብ ሲያስከብሩ በማህበረሰቡም ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸዋል ያሉት ከንቲባዋ ÷ ተመራቂዎች የተሰጣቸውን ሃላፊነት በታማኝነትና በብቃት ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ የንግድ ሥራዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽት 4 ሰዓት እንዲራዘም መወሰኑን አስታውሰው÷ሕዝቡ ያለስጋት አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቀጣይ የከተማዋ ደንብ ማስከበር ሥራ ዘመኑን የዋጀ እና ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ