Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኦሞ ዞን በወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ሙላትና በቱርካና ሃይቅ መስፋፋት የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በትብብር እየተሰራ ነው።

በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በኦሞ ወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።

መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በቱርካና ሃይቅ መስፋፋትና በኦሞ ወንዝ ሙላት ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ከስጋት ቀጣና ነጻ በሆነ አካባቢ የማቋቋም ሥራ እየተከናወነ ነው።

አሁን ላይ በዳሰነች ወረዳ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙና 34 ቀበሌዎች ደግሞ በውሃው መስፋፋት ምክንያት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን አንስተዋል።

የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷የሃይቁን የመስፋፋት አቅም ለመቀነስና አቅጣጫ አስቀይሮ ስጋት በማይፈጥር ስፍራ ሰው ሰራሽ ሐይቅ በመስራት አደጋውን ለመቀነስ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ግድብ በመገንባት የመኖሪያ መንደሮችን ለመከላከል በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሶስት ቦታ እንዲደራጁ መደረጉን እና ምግብን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ማሕበራዊ ተቋማት እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

በመጠለያ ማዕከላቱ ወረርሽኝ እንዳይከሰት አስፈላጊው ክትትልና ክትባት እየተሰጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንደሻው ጣሰው ናቸው።

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.