Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በተኪ ምርት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ማዳን ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተኪ ምርት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል አለ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ አሕመድ ኢድሪስ ለፋና ደጂታል እንዳሉት ÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ከማነቃቃት አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

በንቅናቄው በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የብድር፣ የመስሪያ ቦታ፣ የሃይልና የግብዓት አቅርቦት አንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በተኪ ምርቶች ላይ ለተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ተገቢው ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት ሃላፊው ÷ በዚህም አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በክልሉ 107 ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ከውጪ ይገቡ በነበሩ 95 የምርት አይነቶች እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡

በዚህም 4 ሚሊየን ቶን በላይ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.