Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ከፍ የሚያደርጉ ተግባራት በባህልና ኪነጥበብ ዘርፎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የሚገነቡ የኪነጥበብ ስራዎች በተለያዩ የዓለም ሀገራት የማቅረብ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ከፍ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት በባህልና ኪነጥበብ ዘርፎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህም የኢትዮጵያን ብዝሃ ባሕልና የጥበብ ስራዎችን በማስተዋወቅ ገጽታን የመገንባት ተግባራት በስፋት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ በተለይ በሰርከስ እና በስዕል ዘርፍ በትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች የሀገር መልካም ገጽታ ደምቆ እንዲታይ ያስቻሉ ስራዎች መሰራታቸውን ለአብነት አንስተዋል።

የሀገርን መልካም ገጽታ የመገንባት ስራው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተው፤ በቅርቡም የኢትዮጵያን ቱባ ባህል የሚያስተዋውቅ የባህል ቡድን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት እንደሚጓዝ ተናግረዋል።

የባህል ቡድኑ የብሔር ብሔርሰቦችን ሙዚቃ፣ ጭፈራ እና ባህላዊ አልባሳት በተለያዩ የአፍሪካ፣ አውሮፓ እና ኤዥያ ሀገራት በመጓዝና በማሳየት ትልቅ የባህል ዲፕሎማሲ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

መንግስት ለጥበብ ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በሰራው ስራ የዘርፉን ጥያቄ መመለስ ተችሏልም ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ በዘርፉ ሲነሱ የነበሩ በርካታ ጥያቄዎች መመለሳቸውንም አንስተዋል።

በዘርፉ የነበሩ የመሰረተ ልማት አለመሟላት እና ሌሎች ተያያዝ ችግሮች መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከፈታቸው መካከል መሆናቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዚህም በሀገሪቱ በርካታ አምፊ ትያትሮችና ምቹ የትያትርና የሙዚቃ ማቅረቢያ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኪነጥበብ ዘርፍ ካሪኩለም ተቀርጾ ከታች ጀምሮ በትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ መደረጉ ሌላው የትኩረቱ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ ተግባራት የኪነጥበቡ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች መፍጠራቸውን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቅርቡም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ መድረክ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.