የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
እየተካሄደ በሚገኘው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር ያለመ የባለድርሻ አካላት መድረክ ላይ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ሀደራ አበራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ ጥቅል ዲፕሎማሲ ምሰሶ ነው ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅሞች ከውጩ ዓለም ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ አስረድተው፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና ለኢንቨስትመንት ዘርፍ አዲስ ዕድልን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በማሻሻያው በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በርካታ የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ በርካታ የሥራ ዕድሎች መፍጠር መቻሉን ነው ያስገነዘቡት።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ሀገራት እየሠሩ ያሉ ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን መሳብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ