Fana: At a Speed of Life!

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በሥራ እድል ፈጠራ ዘርፍ አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በሥራ እድል ፈጠራ ዘርፍ አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው አሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረው ስለኢትዮጵያ የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና ጸጋ በመለየት የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

ለዚህም ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና አይሲቲ ዘርፎች ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለሥራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው÷ እስካሁንም አበረታች ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የግል ዘርፉን የሥራ እድል ፈጠራ ሒደት ይበልጥ ለማስፋት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአዲሱ ምልከታ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ከዕለት ጉርስ ባለፈ ሃብት ፈጠራ ላይ መሰረት ያደረገ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ሚኒስቴሩ የክህሎት ልማት እና የተቋም ግንባታ ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።

በመድረኩ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አሕመድ÷ የግሉን ዘርፍ የሥራ እድል ፈጠራነት ለማጠናከር በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ዘመኑ ያፈራቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ለወጣቶች ክህሎት መር ሥልጠና መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዜጎች ከተቀጣሪነት ይልቅ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም ተገልጿል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.