Fana: At a Speed of Life!

ሰላም እንዲመጣ ባለሃብቶች ታጣቂዎችን በገንዘብ መደገፍ ማቆም አለባችሁ –  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ሰላም የሚፈልጉ ባለሃብቶች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎችን በገንዘብ መደገፍ እንዲያቆሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው ሀገሪቱ ከተውጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ መንግስት ለሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

በጫካ ያሉ ታጣቂዎችን እየቀለበ 60 በመቶ የኢትዮጵያን ሰላም የሚያናጋው የኢትዮጵያ ሃብታም ነው በማለት ገልጸው፥ ታጣቂዎችን በገንዘብ እየደገፉ መንግስት ሰላም እንዲያመጣ መጠየቅ ትክክለኛ አካሄድ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡

ባለሃብቶች እውነተኛ ሰላም ፈላጊ ከሆኑ በጫካ ያሉ ኃይሎችን መደገፍ አቁመው ወደ ሰላም እንዲመጡ መምከር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ሰላም የሚፈልግ ካለ በእኛ በኩል ዝግጁ ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት በሰላም የሚመጡ አካላትን ተቀብሎ ለማወያየት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ህግ ማስከበር የመንግስት ስራ በመሆኑ መቀጣት ያለበትን አካል መቅጣት እንደሚገባ ገልጸው፥ ሰላም በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ተባብረን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሰላምን በተመለከተ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ገልጸው፥ ነገር ግን ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቁ አካላት ራሳቸውን በማግለል የመንግስት ብቻ ጉዳይ የማድረግ ልምምዶች ተገቢ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግስት ኮንትሮባንድን እና ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ባዘጋጃቸው የፍተሻ ኬላዎች የኮቴ እያሉ ገንዘብ የሚጠይቁ አካላት እንዳሉ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ምላሽ፥ እነዚህ የፍተሻ ኬላዎች የማይኖሩ ከሆነ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች እየገባ የሰዎችን ህይወት እንደሚቀጥፍ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ገንዘብ ሳይጠየቅ ፍተሻ የሚደረግበትን መንገድ ለማመቻቸት መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.