የግብር ክፍያን በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት የሚፈጽሙ ግብር ከፋዮች ቁጥር እያደገ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር የግብር መረጃ እና ክፍያን በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት የሚፈጽሙ ግብር ከፋዮች ቁጥር እያደገ ነው አለ፡፡
በሚኒስቴሩ የመረጃ ቴክኖሎጂ ማዕከል ኃላፊ አቶ ክልሉ ታመነ እንዳሉት ÷ ባለፉት አስር ወራት በኤሌክትሮኒክስ መረጃን የማሳወቅ ሒደት ከ95 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡
በተጨማሪም ከ75 እስከ 80 በመቶ የግብር ክፍያዎች መፈጸማቸውን ኃላፊው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የፌደራል ግብር ከፋዮች መረጃንና ክፍያን ባሉበት እንዲፈጽሙ መደረጉ የግብር አሰባሰብ ሒደቱን እና ሥርዓቱን እንዲቀላጠፍ ማድረጉን አንስተዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓቱን ወደ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ግብር ክፍያ ሥርዓት ለግብር ከፋዩ ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ሠራተኞች የሥራ ጫና መቀነሱን ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በወረቀትና በሰው ሃይል ረጅም ጊዜ ተወስዶ ይሰራ የነበረው አሰራር ከአድካሚነቱ በላይ የሥራ ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደነበረውም አስታውሰዋል።
በማርታ ጌታቸው