Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የግምገማ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ የግምገማ ሥርዓት ላይ ያተኮረው 25ኛው የአፍሪካ ኢቫሉዌሽን አሶሴሽን ጉባኤ ከሰኔ 9 ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ለሦስት ቀናት የሚካሄደውን ጉባኤ የአፍሪካ ኢቫሉዌሽን አሶሴሽን፣ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ኢቫሉዌሽን አሶሴሽን በትብብር ማዘጋጀታቸው ተገልጿል።

ጉባኤውን በተመለከተ በተሰጠው መግለጫ የአፍሪካ የግምገማ ሥርዓት ያለበትን ደረጃ እንዲሁም ከአፍሪካ 2063 አጀንዳ ጋር የተስማማ የግምገማ ሥርዓት እንዲኖር እየተሰራ ስላለው ሥራ ውይይት እንደሚደረግበት ተመላክቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት በአህጉሪቱ የግምገማ ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎች፣ ያገጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ መፍትሄዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግም በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡

በጉባኤው ላይ ከ40 በላይ ሀገራት ተወካዮችና ከ300 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙ የኢትዮጵያ ኢቫሉዌሽን አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ደረጀ ማሞ ተናግረዋል፡፡

መረጃን መሰረት ያደረገ የውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ 14 የግምገማ ጽሑፎች እንደሚቀርቡና 70 ያህል ተናጋሪዎች በውይይቱ ላይ መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ኢቫሉዌሽን አሶሴሽን ባለፉት የ25 ዓመታት የግምገማ ሥርዓትን በአፍሪካ ውስጥ በማስተዋወቅ ትልቅ ሥራ መስራቱን የተቋሙ ፕሬዚዳንት ሚቼ ኦውድራጎ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በበኩላቸው፥ ሚኒስቴሩ የግምገማና ክትትል ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ በማንሳት አሰራሩን የሚያግዝ ፖሊሲ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ኃላፊዎች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በመረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑና መረጃዎችን አደራጅቶ የማቅረብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአፍሪካ 2063 አጀንዳን መሰረት ያደረጉ ዕቅዶችን አውጥቶ እንደሚሰራም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታ አዲስ አበባን እንደሚጎበኙ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ይህም የቱሪዝም ዘርፍ የሚያነቃቃ መሆኑን አንስተዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.