ሀገር በቀል ጥናትና ምርምሮች ለህብረተሰብ ጤና ግብዓትነት እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል ጥናትና ምርምሮችን ወደ ልማት በመቀየር ለህብረተሰብ ጤና ግብዓትነት ማዋል ይገባል አሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ።
አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (አህሪ) ‘የላቀ የጤና ምርምርና ልማት ለተሻለ ጤና’ በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው::
ሚኒስትር ደኤታዋ በመድረኩ እንዳሉት፤ በተለያዩ መንገድ የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች በተገቢው ወደ ልማት ሲቀየሩ አይታይም።
አህሪ በ55 ዓመታት ሳይንሳዊ ጉዞው ውስጥ ከምርምር ባለፈ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ይህን ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠልና የተሰሩ ምርምሮችን ወደ ሕዝብ ለማድረስ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአህሪ ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀምና በጋራ በመቆም ድህነትን ጨምሮ ሀገርን ወደኋላ የሚያስቀሩ ችግሮችን መቅረፍ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።
የጤናው ዘርፍ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል በቂ አቅም እንዳለ ጠቅሰው፤ አህሪ ከበርካታ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራቸው ያሉ ሳይንሳዊ ተፅእኖዎች በአብነት አንስተዋል።
የምርምር ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ከመተግበር ባለፈ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግሮች እየተደረጉ እንደሆነ በመግለጽ፤ በቀጣይ በጤና ምርምር፣ ልማት፣ ፈጠራ እና ስልጠና ላይ ተቋሙ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አህሪ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር፣ የባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒቶች ምርምርና ልማት፣ የክትባት መመርመሪያና የህክምና መሳሪያዎች ምርምር ልማትና ምርትን ጨምሮ የጤና ፓሊሲዎች ማሻሻያ ግብአቶችን ለማመንጨት በስፋት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ለሥጋ ደዌ በሽታ የሰውነት የመከላከል ኃይል ሳይንሳዊ ምርምርን መነሻ አድርጎ ሥራ መጀመሩ ተመላክቷል።
በዘቢብ ተክላይ