አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ለተግባራዊ የአየር ንብረት መፍትሄዎች ቁርጠኛ መሆኗን ማሳያ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ለተግባራዊ የአየር ንብረት መፍትሄዎች ያላትን ጥልቅ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር 2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በፈረንጆቹ ከመስከረም 8 እስከ 10 ቀን 2025 እንደምታስተናግድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ጉባኤው ለአፍሪካ የአየር ንብረት ስትራቴጂ ቁልፍ የሆነውን ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መፍትሄን ማጠናከር፣ አህጉሪቱን ዳግም አረንጓዴ ማልበስና የአፍሪካ አንድነትን ማጎልበት ላይ በማተኮር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጪው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዝግጅት እያደረገች መሆኑን አንስተው፥ ይህም ለተግባራዊ የአየር ንብረት መፍትሄዎች ያላትን ጥልቅ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
መልዕክቱ ግልጽ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተፈጥሮ ላይ መስራት፣ የመፍትሄ አማራጮችን ማሳደግና ኢኮኖሚውን የሚመራ ስነ ምህዳር መፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ለመቀበል ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡