Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም የግብርናውን ዘርፍ የሚያዘምኑ ተግባራት እያከናወነ ነው – ፍሬሕይወት ታምሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ ነው አሉ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ፡፡

ኢትዮቴሌኮምና የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ በግብርናው ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በዚህ ወቅት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ÷ የግብርናውን ዘርፍ ለማገዝ ቀደም ሲል የግብርና እሴት ሰንሰለትን ከምርት እስከ ገበያ የሚያስተሳስር ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለአርሶ አደሩ ፋይናንስ ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ የዲጂታል ሥራዎች መከናወናቸው ገልፀዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር የተደረሰው የስማርት ግብርና ስምምነት ዘርፉን በማዘመን አርሶ እና አርብቶ አደሩ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ እንዲሁም አዳዲስ የሥራ ዕድሎችም እንዲፈጠሩ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱ የግብርናውን ዘርፍ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እና በዘርፉ ያለውን ሰንሰለት ለማስተሳሰር እንዲሁም በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፥ ግብርናን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እና ዘመናዊ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረሰው የትብብር ስምምነትም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱ አርሶ አደሩ የወቅቱን የገበያ ዋጋ ጨምሮ በርካታ መረጃዎችን የሚያገኝበት እንዲሁም ከባህላዊ ግብርና ወደ ዕውቀት ተኮር ግብርና የሚያሸጋግር እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.