Fana: At a Speed of Life!

ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤ ምሲ) ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን እና የግል ዘርፉን ሚና ለማጠናከር ያለመ “ኢኮትሬድ” የተሰኘ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል፡፡

ፕሮጀክቱ “በግሉ-ዘርፍ የሚመራ የእሴት ሰንሰለትን በማሳደግ የኢትዮጵያን ንግድና ምጣኔ ሃብት ትስስር ማጎልበት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚተገበረው።

የንድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት ÷ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አማካይነት ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ለማሳለጥ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ሚና አለው፡፡

ከዚህ ባለፈም የግሉን ዘርፍ ሀገራዊ ሚና ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው ያስገነዘቡት፡፡

በቀጣይ 5 ዓመታት የሚተገበረው ፕሮጀክቱ ቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለቶችንና ተቋማዊ አቅምን ማሳደግ እንዲሁም የንግድ ተቋማትን ማጎልበት ላይ ያተኩራል፡፡

የአፍሪካን ንግድ ልውውጥ ከ11 በመቶ ወደ 33 በመቶ ለማሳደ፣ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግርን ለማጠናከር እንዲሁም ታሪፎችን እና የንግድ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተጠቅሷል፡፡

በመድረኩ ካሳሁን ጎፌን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኤመስበርገር፣ የዘርፉ ምሁራን እና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል፡፡

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.