ዜጎች በንጹህና ጤናማ አካባቢ ለመኖር የሚያስችላቸውን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዜጎች በንጹህ አካባቢ የመኖር መብታቸው ሊረጋገጥ ይገባል አሉ።
በክልሉ 2ኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፤ የተጀመረውን ሀገራዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ ዜጎች በንጹህና ጤናማ አካባቢ መኖር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል።
በተለይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የፕላስቲ ብክለት ለመግታት የወጡ ህጎችን በመተግበር ችግሩን መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሀገር ደረጃ የተጀመሩ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር ብክለትን በዘላቂነት ለመግታት መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።
ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ ውጤት እያመጣ መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው፤ ‘ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ’ በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር ደረጃ በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።
የብክለትን አስከፊነት የማስገነዘብ፣ ህጎችና መመሪያዎች እንዲሻሻሉ የማድረግ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ዘንድሮ በሚካሄደው 2ኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የህግ ተከባሪነትን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ ግዛቴ ግጄ በንቅናቄው የፕላስቲክ፣ የአፈርና ውሃ፣ የአየር፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ የድምጽ ብክለትን የመከላከል እንዲሁም መወገድ ያለባቸውን ኬሚካሎችና ኤሌክትሮኒክስ የማስወገድ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዚህም 5 ነጥብ 5 ሚሊየን የክልሉ ህዝብ ስለብክለት ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ዜጎች በንጹህና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብታቸውን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል ነው ያሉት።
በመለሰ ታደለ