በኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ሥራዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል – የተባበሩት መንግስታት
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለዘላቂና ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የተባበሩት መንግስታት፡፡
የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ የተለያዩ ዘላቂ የልማት ሥራዎችን መደገፍ የሚያስችል የ6 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የተባበሩት መንግስታት ረዳት ዋና ጸሃፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላካባሮቭ (ደ/ር) እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው ፈርመውታል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ ልማት ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ ነው፡፡
ድጋፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለኢነርጂ ልማት፣ ለትምህርት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ለሌሎች ዘርፎች ይውላል፡፡
ራሚዝ አላካባሮቭ (ዶ/ር) ÷ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው÷ የትብብር ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የተባበሩት መንግስታት እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው÷ለስምምነቱ ውጤታማነት በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡