የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 989 ተማሪዎች በዓድዋ ድል መታሰቢያ እያስመረቀ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በሦስተኛ፣ በሁለተኛ እና በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ያስተማራቸውን ተማሪዎች ነው እያስመረቀ የሚገኘው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ መንግስት በእውቀት የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በእውቀት የበለጸገ ምክንያታዊና ትጉህ ዜጋ ለሀገር ዘላቂ እድገት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፥ በዚህ ረገድ የለውጡ መንግስት ጥራቱ የተረጋገጠ እውቀት ያለው ቁርጠኛ ትውልድ እንዲፈጠር በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ገልጸው፥ ለትውልዱ ከዕዳ ይልቅ ምንዳን ለማውረስ በእውቀት የበለፀገ ዜጋ ጉልህ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት