ምንም አይነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪም ሆነ የአቅርቦት እጥረት የለም – ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምንም አይነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪም ሆነ የአቅርቦት እጥረት የለም አለ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ÷ የነዳጅ አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው ችግር ባልተገባ መንገድ በተሰራጨ የተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተፈጠረ ነው ብለዋል።
በግንቦት ወር መንግስት የነዳጅ ጥቅል ድጎማን ማንሳቱን አስታውሰው ÷ ነገር ግን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ድጎማውን በተመለከተ የተዛባ መረጃ ተሰራጭቷል ነው ያሉት።
ይህን ተከትሎም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል የሚል ሃሳብ እንዲኖር ማድረጉን እና በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት የነዳጅ እጥረት እንዳለ ለማስመሰል ሙከራ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ምንም አይነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንደሌለ እና ይህንን ተከትሎ በአቅርቦቱ ላይ እክል በሚፈጥሩ አካላት ላይ ክትትልና ርምጃ መውሰድ ጀምረናል ብለዋል።
በዚህም ከፈቃድ መንጠቅ እና ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ባለፈ በማደያ ባለቤቶች ላይ ከ2 እስከ 5 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚተላለፍ አሳስበዋል።
በመዲናዋ አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ርምጃ መውሰድ መጀመሩን ጠቁመው ÷ ወደ ከተማዋ በተቀመጠላቸው ጊዜ መግባት የነበረባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት