Fana: At a Speed of Life!

ሆስፒታሉ የሕብረተሰቡን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው።

የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፈዬራ ዲንሳ (ዶ/ር) ÷ ተቋሙ ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋና የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበረውን የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል አሁን ላይ ተመራጭ የሕክምና ማዕከል ማድረግ መቻሉን ጠቁመው÷ የሕብረተሰቡን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

የሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ም/ዳይሬክተር ዶ/ር መስፍን ጣፋን በበኩላቸው ÷ ሆስፒታሉ በቀን 500 ሰዎችን በማስተናገድ ከ3 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።

በዚህም የኩላሊት እጥበትና የካንሰር ሕክምናን ጨምሮ በሁሉም አይነት እና ደረጃ ያሉ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ በተሟላ መንገድ እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት÷ ሆስፒታል በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ መተዳደር ከጀመረ ወዲህ አገልግሎቱ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሉንና እስፈላጊውን ሕክምና በተገቢው መንገድ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

በዚህም የተሻለ አገልግሎት፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሁሉን አቀፍ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን አመልከተዋል።

በሪፈር የተሻለ ሕክምና ለማግኘት በከፍተኛ ወጪ እና ድካም ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዳስቀረላቸውም ነው ያስረዱት፡፡

በሲፈን መገርሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.