Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል  –  ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እና ተቋማት ተቀባይነት እንዲኖረው በትብብር መስራት ይገባል አሉ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ተመራማሪ አዲስ አለማሁ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ለበርካታ ዓመታት አይነኬ የነበረው የባሕር በር ጥያቄ በለውጡ መንግስት መነሳቱ የሚደነቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉን አንስተው ÷ይሁን እንጂ ጥያቄው በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው የተከናወኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች አጥጋቢ አይደሉም ብለዋል፡፡

ጥያቄው ፍትሃዊ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የሚፈቀድ እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብት መሆኑን ያስረዱት ተመራማሪው ÷ በአንጻሩ  አጀንዳውን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ የተደረገ ጥረቶች ውስን መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አጀንዳው እንደ ኢጋድ፣ አፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት በመሳሰሉ ተቋማት እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት እና መንግስታት ተቀባይነት እንዲኖረው የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ምሁራን፣ ዲፕሎማቶች፣ መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አጀንዳውን የአንድ ሰሞን ብቻ ከማድረግ ይልቅ የባሕር በር ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ አቶ ሴኔሳ ደምሴ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያ ፍትሃዊ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ጉዳዩ ይበልጥ ቅቡል እንዲሆን ተጨማሪ ጥረት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሴነሳ÷ እንደነውር ሲታይ የነበረው የባሕር በር ጥያቄ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ መቻሉ በራሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፍትሃዊ የባሕር በር ጥያቄውን በጥናትና ምርምር በመታገዝ እንዲሁም በተደራጀ የጋራ ጥረት ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ማስረዳት እንደሚገባ ነው ያብራሩት፡፡

የባሕር በር ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅምን ያስጠብቃል ያሉት ምሁራኑ ÷ አጃንዳውን ለማሳካት የፐብሊክ ዲፕሎማሲን አማራጭ ማድረግ አንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.