Fana: At a Speed of Life!

ግልገል ጊቤ ሦስት 7 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል አመነጨ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ 7 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቷል አሉ የግድቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ሰሙ።

አቶ ሃብታሙ እንዳሉት ÷ ግልገል ጊቤ ሦስት ኬንያን ጨምሮ ለቀጣናው ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቡ የታዳሽ ኃይልን በማሳደግና የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም አገልግሎት የጀመረው ግድቡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ የሚገኝ ግዙፉ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ግድቡ 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን÷ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የግልገል ጊቤ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት 50 በመቶ በመሸፈን ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በማቅረብ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡

የኃይል ማመንጫ ግድቡ የሥራ ሒደት በኢትዮጵያውያን ብቁ ባለሙያዎች እየተመራ መሆኑን ጠቁመው÷እያደገ ለሚገኘው ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ምላሽ በመስጠት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

በተያዘው ዓመትም 7 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.