Fana: At a Speed of Life!

“ጋዜጠኞች ቅጥፈትን እንጂ በትህትና እና በእውቀት መተቸት አልተከለከሉም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚዲያ ባለሙያዎች ጉዳዮችን በትህትና እና በእውቀት ሊተቹ እና ሊጠይቁ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብና የግል ሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት እንደተናገሩት ፥ ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን ተስፋና ነገ በማሰብ በእውነት፣ በእውቀት፣ በትህትና፣ በጥበብና በትጋት ያለውን ነገር የማሳየት ሥራ ሊሰሩ ይገባል።

ሚዲያዎች ሊተቹ እና ሊጠይቁ እንደሚገባ አንስተው÷ በአንጻሩ ሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት እና ከብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጋጭ ሥራ መስራት እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎች መሰል ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊገጥማቸው ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይሁን እንጂ ይህ የመንግስት አቋም አይደለም ብለዋል፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎች በሥራ ሒደት የሚያጋጥሟቸውን መሰል ችግሮች በትዕግስት ማሳለፍ እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

ጋዜጠኞች በተገቢው መንገድ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ለማስቻል ከሚታወቅ ተቋም ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ከያዙ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊው ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚያግዝ ሥራ መስራት፣ ሕዝቡን ማንቃት እና ማስተማር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

መንግስት የሚጠበቅበትን ማከናወን ሲሳነውም በትህትና እና በእውቀት ተመስርቶ መተቸት እንደሚያስፈልግ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ጋዜጠኞች የሀገርን ጥቅም ለማስከበር እስከሰራችሁ ድረስ በእኛ በኩል ተባብሮ ለመስራት፣ ሕግ ለማሻሻል፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት እና በፋይናንስ ለመደገፍ ፍላጎት አለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.