የባሕር ዳር ከተማ ኮሪደር እና የጣና ዳርቻ ልማት…
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባሕር ዳር ከተማ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት እና ከተማዋን ከጣና ሐይቅ ጋር የማስተሳሰር ልማት ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ሥራ ነው።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የተወያዩ የሕዝብ እና የግል ሚዲያዎች እንደሁም የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች አዲሱን የዓባይ ድልድይ፣ የኮሪደር እና ከተማዋን ከጣና ሐይቅ ጋር የማስተሳሰር የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት÷ ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ማድረግ የሚያስችል ተግባራት ተከናውነዋል።
የልማት ሥራዎቹ የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት ይበልጥ ለማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰው÷ ልማቱ የተከናወነበት ፍጥነት እና ጥራት ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በባሕር ዳር ከተማ እየተመዘገበ ያለውን የልማት ውጤት በማስተዋወቅ በኩል የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው÷የሚካሄደው የልማት ሥራ ከተማዋን ዘመናዊና ተመራጭ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በኮሪደር ልማት እና ከተማዋን ከጣና ሐይቅ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት፡፡
ከተማዋ ከተፈጥሮ ፀጋዋ ባሻገር የዓባይ ድልድይ እና የመንገድ ዳር ልማቱ የበለጠ የቱሪስት ከተማ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያ የነበሩ አካባቢዎች ለምተው የሕዝብ መናፈሻ በመሆን ማህበራዊ መስተጋብርን እያጠናከሩ ይገኛሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከአስፋልት መንገድ፣ እግረኛና ብስክሌት መተላለፊያ መንገድ ባሻገር የአረንጓዴ ልማት፣ የሰዎች ማረፊያ፣ መዝናኛና ሌሎች ግንባታዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል፡፡
በዐቢይ ጌታሁን