በእስራኤል ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነሳ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እስራኤል ከኢራን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሷን ተከትሎ በሀገሪቱ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቷል፡፡
እስራኤልና ኢራን ባለፉት 12 ቀናት ባካሄዱት ጦርነት እስራኤል “ኦፕሬሽን ራይዚንግ ላየን” በሚል ዘመቻ የኢራን የኒውክሌርና ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
አሜሪካ ጣልቃ ገብታበት በነበረው የሀገራቱ ጦርነት በርካታ ሰዎችን ለሕልፈት የዳረገ ሲሆን÷ መጠነ ሰፊ የንብረት ጉዳት ማስከተሉንም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በጦርነቱ እስራኤል የኢራን አብዮታዊ ዘብ አመራሮችና የኒውክሌር ተመራማሪዎች ላይ ርምጃ ከመውሰድ ባለፈ የሀገሪቱን የኒውክሌር መሰረተ ልማት ማውደሟ ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ ኢራን በሰጠችው አጸፋ የሞሳድን ቢሮ ጨምሮ ከ60 በላይ በሚሆኑ የእስራኤል ተቋማት ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟ ነው የተጠቀሰው፡፡
ሀገራቱ ባደረጉት የ12 ቀና ጦርነት በኢራን ከ400 በላይ ዜጎች ለሕልፈት ሲዳረጉ ከእስራኤል ደግሞ 28 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ለቀናት ከዘለቀው ጦርነት በኋላ ሀገራቱ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሸማጋይነት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት መምጣታቸውን ተከትሎ እስራኤል ጥላው የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስታለች፡፡
የተኩስ አቁሙ ከተደረገ ሰዓታት በኋላ በእስራኤል የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ የተመለሱ ሲሆን ÷ የቤን ጎሪዮን አየር መንገድ መደበኛ በረራ መጀመሩን ታይምስ ኦፍ እስራል ዘግቧል።
በሚኪያስ አየለ