የዋጋ ግሽበትን ወደ 14 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል – ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በተገባደደው በጀት ዓመት የዋጋ ግሽበትን ወደ 14 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል አሉ።
አቶ ማሞ የብሔራዊ ባንክ የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል።
በዚህ ወቅትም ብሔራዊ ባንክ ባለፉት 11 ወራት የተገበረው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ግሽበትን መቀነስ አስችሏል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም በጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ባለፉት11 ወራት ለመንግስት ይሰጥ የነበረውን የብድር ምጣኔ ወደ ዜሮ ማውረድ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡
ብሔራዊ ባንክ ውጤት ካስመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም በትይዩ ገበያና በባንኮች የውጭ ምንዛሪ መካከል የነበረውን ልዩነት ማጥበብ እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ አስተዳደር አጠቃላይ ገቢን ወደ 32 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ከፍ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማሳደግ፣ ለግል ዘርፎች የሚቀርበውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መጨመር፣ ዕዳ የመክፈል አቅምን የማሳደግና መሰል ትሩፋቶች መገኘታቸውንም አብራርተዋል፡፡
በሔብሮን ዋልታው