ብሔራዊ ቤተመንግሥትና አንድነት ፓርክ ተደብቀው የቆዩ ቅርሶችን የገለጡ ናቸው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ሽማግሌዎች ብሔራዊ ቤተመንግሥትና አንድነት ፓርክ ተደብቀው የቆዩ የኢትዮጵያውያን ቅርሶችንና የማንነት መገለጫዎችን በውብ ገፅታ ለዓለም የገለጡ ናቸው አሉ።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች አንድነት ፓርክና ብሔራዊ ቤተመንግሥትን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡ የሀገር ሽማገሌዎች፥ መንግሥት የኢትዮጵያን ውብ ቅርስና ታሪክ በማደስ የሚያኮራ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ ለትውልድ የሚሻገሩ ድንቅ የልማት ሥራዎችን ማየታቸውን አንስተው፥ አንድነት ፓርክና ብሔራዊ ቤተመንግሥት የኩራት መገለጫዎቻችን ናቸው ብለዋል።
የተሰራው ሥራ ለዘመናት ተደብቀው የቆዩትን ቅርሶች እና የኢትዮጵያን የስልጣኔ ታሪክን አጉልቶ ለዓለም የገለጠ በመሆኑ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸው፤ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ ባህልና ቅርስ በአንድ ላይ አካተው የያዙ መሆናቸውም የሀገራዊ አንድነት ምልክት እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ በአግባቡ ሰንዶ ማስቀመጥ ያስቻለ እንዲሁም እድሳቱ ታሪክና ቅርስ እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ማሳቱን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ውብና ጽዱ ሆና በማየታቸው መደነቃቸውን ጠቅሰው፤ አዳዲስ ልማቶችንና ነባር ቅርሶችን በአንድነት ያሰናሰለ ድንቅ የልማት ሂደት እንደተመለከቱ ነው የተናገሩት።
ይህ የኢትዮጵያን ከፍታ ዕውን በማድረግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ያለው የልማትና የቅርስ ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።