Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ44 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ44 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል አለ።

በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ በተቀናጀ ግብርና ልማት ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል የቡና ምርታማነት ማሳደግ ተጠቃሽ ነው።

በዚህም የክልሉን የመልማት ፀጋ መነሻ በማድረግ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቡና ችግኝ ተከላን ለማስፋፋት በርካታ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ የቡና ልማትን በቤተሰብ፣ በመንደር፣ በክላስተር እና የቡና ልማት ኮሪደር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አንስተው÷ ከ44 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ ተዘጋጅቶ ከ63 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የተከላ ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለያዩ ክልላዊ የቡና ልማት ኢኒሼቲቮች በተሰራው ስራ የቡና ልማት ውጤታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በክልሉ በባህር ዛፍ ተይዘው የነበሩ ማሳዎች በቡናና ፍራፍሬ የመቀየር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በክልሉ ከ158 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቡና መሸፈኑን ያነሱት አቶ ኡስማን÷ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልሉ የቡና ልማት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመላክተዋል።

በተለይም ከዚህ ቀደም ቡና በማብቀል የማይታወቁ አካባቢዎች ጭምር በአረንጓዴ አሻራ ቡና ወደ ማምረትና ማልማት በስፋት መጠቀም መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በቡና ልማት ውስጥ ከችግኝ ዝግጅት እስከ ቡና ማምረትና ግብይት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቁመው÷ በተለይም የሴቶች ድርሻ ትልቁን ቦታ ይይዛልም ነው ያሉት።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.