Fana: At a Speed of Life!

ከኢንዱስትሪ ፓርኩ የአቮካዶ ዘይት ምርት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለውጭ ገበያ ካቀረበው የአቮካዶ ዘይት ምርት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኃይሉ የተራ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው የክላስተር ማዕከላት የውጭ ምንዛሪን የሚያስቀሩ ተኪ ምርቶችን እያቀረቡ ነው።

ባለፉት 11 ወራት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ለሚገኙ አራት የአቮካዶ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከ12 ሺህ ቶን በላይ ጥሬ ምርት መቅረቡን ገልጸው፥ 389 ነጥብ 28 ያለቀለት የአቮካዶ ዘይት ተመርቷል ብለዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 320 ቶን ድፍድፍ የኦቫኮዶ ዘይት ለውጭ ገበያ ቀርቦ 2 ሚሊየን 299 ሺህ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በክልሉ በአምስት ከተማ አስተዳደሮች ክላስተር ማዕከላትን በማልማት እንደሚያስተዳድር ገልጸዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፥ ከክላስተር ማዕከላቱ ለገበያ በቀረቡ ተኪ ምርቶች በየዓመቱ በአማካይ ከ9 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል፡፡

ለአብነትም ባለፉት 11 ወራት ከ576 ነጥብ 8 ቶን በላይ ያለቀላቸው የወተት፣ የማርና የቡና ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ቀርበው 29 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

አቶ ኃይሉ እንደገለጹት፥ ባለፉት አራት ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ በአቮካዶ ዘይት 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በሌሎች ተኪ ምርቶች 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተገኝቷል፡፡

በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ስምንት ፕሮጀክቶች በአቮካዶ፣ በወተት፣ በማር፣ በቡና እና ጁስ ምርቶች ማቀነባበር ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

በተደራጁ ማህበራት አማካኝነት ከ136 ሺህ 400 አርሶአደሮች ጋር የምርት ትስስር መፈጠሩን ገልጸው፥ 25 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.