በክልሉ ሊከሰት ለሚችል የመሬት መንሸራተት አደጋ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የክረምት ዝናብን ተከትሎ ሊከሰት የሚችል የመሬት መንሸራተትና ጎርፍ አደጋ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው።
የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ለማ መሰለ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በዘንድሮው ክረምት ለአደጋ ተገላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ወረዳዎችን የመለየት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡
በዚህም በክልሉ ከሚገኙ 41 ወረዳዎች 22 ወረዳዎች ውስጥ ተገላጭ የሆኑ ቀበሌዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን ነው ያስረዱት፡፡
የመሬት መንሸራተት ምልክት የሚሆኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።
የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን በተለያዩ መንገዶች በማከናወን የዝናብ ሁኔታው ከመጠን በላይ ከሆነ ሕብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ቀድሞ ከአካባቢው የማሸሽና መጠለያ ቦታዎችን የማመቻቸት ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በቤንች ሸኮ ዞን 89 አባዎራዎች፣ ካፋ ዞን 40 አባዎራዎች እንዲሁም በኮንታ ዞን 16 አባዎራዎች ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን በማረጋገጥ ካሉበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ለማዛወር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ የመሬት መንሸራተት አደጋ በመስከረምና ጥቅምት ወራት ላይ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመው ÷ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን በመከታተል እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር የክትትል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም በሕብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን የጉዳት መጠን ለመቀነስና ለመከላከል መሬት ላይ ያለው ሁኔታ በየጊዜው እየተገመገመ መሆኑን የገለጹት ለማ (ዶ/ር) ÷ የክረምቱ ዝናብ ከመጠን በላይ ከሆነ ከ20 እስከ 25 ሺህ ዜጎችን ሊያፈናቅል እንደሚችል አመልክተዋል።
ሕብረተሰቡም ዝናብ በሚበዛበት ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የመከላከል ሥራዎችን እንዲያከናውንና የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲተገብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአድማሱ አራጋው