የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ ቋሚ የእንክብካቤ ስራ መስራት ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በቋሚነት በማከናወን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ማሳደግ ይገባል አሉ።
አቶ አደም ፋራህ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ቆላ ሙልአቶ ቀበሌ የሌማት ትሩፋት የማር መንደር ጎብኝተው ተደራጅተው ንብ የሚያንቡ ወጣቶችን አበረታትዋል።
በጉብኝቱ ወቅት አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፤ የተጎዱ መሬቶች በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ሲለወጡ ቋሚ የእንክብካቤ ማድረግ ይገባል።
ይህም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚያስችል ውጤት እንደሚያመጣ አስገንዝበዋል።
አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ በክልሉ በተከናወነ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በተለይም በእንስሳት ተዋፅኦ ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የህብረተሰቡን የስነ-ምግብ ስርዓት ያጎለብታል በማለት ገልጸው፤ በዚህ ረገድ የሌማት ትሩፋት አስተዋጽኦ እያበረከ መሆኑን ጠቁመዋል።
መርሐ ግብሩ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ ገበያ የማረጋጋት እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማሳደግ ሰፊ ግብ አንግቦ በመተግበር ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በመለሰ ታደለ