ከተቹት ውድድር የተሰናበቱት ፔፕ ጋርዲዮላ …
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር በተለያዩ አካላት በርካታ ትችት እየተሰነዘረበት ይገኛል፡፡
ውድድሩን ሲተቹ ከነበሩት መካከል የማንቼስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ አንዱ ቢሆኑም በሳዑዲው ክለብ አልሂላል ተሸንፈው ከውድድሩ ተሰናብተዋል፡፡
በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ ጨዋታውን አሸንፎ ሩብ ፍፃሜውን ይቀላቀላል ተብሎ ቢጠበቅም በሲሞኒ ኢንዛጊ በሚመራው የሳዑዲው ክለብ አል ሂላል ተሸንፎ ከውድድሩ ለመሰናበት ተገድዷል፡፡
ከጥሎ ማለፉ ጨዋታ አስቀድሞ ውድድሩን ሲተቹ የነበሩት አሰልጣኙ ጉዟቸው ከዚህ ሊሻገር አልቻለም፡፡ ጋርዲዮላ በዚህ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠማቸው ሽንፈት ሲሆን÷ አል ሂላል በበኩሉ ሲቲን ከውድድሩ በማሰናበት ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡
ፔፕ ጋርዲዮላ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር ተጫዋቾቻችንን ለጉዳት ከመዳረጉም ባለፈ ቀጣዩ የውድድር ዓመታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድርብናል ሲሉ ውድድሩን መተቸታቸው አይዘነጋም፡፡
የማንቼስተር ሲቲው አለቃ ፔፕ ጋርዲዮላ ውድድሩን ቢተቹትም ጥሎ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
የቀድሞ የሊቨርፑል አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድርን ከተቹት መካከል አንደኛው ሲሆኑ÷ ውድድሩን የመጀመር ሐሳብ በእግር ኳስ ካየናቸው መጥፎ ውሳኔዎች መካከል የከፋው ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ውድድሩ አላስፈላጊ ነው ያሉት የርገን ክሎፕ÷ ተጫዋቾችን ላልታሰበ ጉዳት የሚዳርግና ጠቀሜታ የሌለው ነው ብለዋል፡፡
ሌላው ይህንን ውድድር ከተቹ ሰዎች መካከል የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ይገኙበታል፡፡ በኢንዞ ማሬስካ የሚመራው ቼልሲ በውድድሩ ሩብ ፍፃሜውን መቀላቀል ቢችል አሰልጣኙ ግን አሜሪካ ለእግር ኳስ ትክክለኛ ቦታ አይደለችም ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ቼልሲ ከቤኔፊካ ጋር ባደረገው የጥሎ ማለፍ ውድድር÷ ጨዋታው ለሰዓታት ተቋርጦ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የቼልሲው አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት ጨዋታውን ማቋረጥ ተገቢ እንዳልሆነ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከምድብ ጨዋታዎች ጀምሮ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ምክንያት እየተቆራረጠ የሚገኘው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር አሁንም ፍፃሜውን እስኪያገኝ ድረስ የጨዋታ መቆራረጥ እንዳይኖር የሁሉም ስጋት ነው፡፡
የተጠበቀውን ያህል ተመልካች ማግኘት ያልቻለው እና በተለያዩ አካላት ትችቶች እየተሰነዘሩበት የሚገኘው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር እስከ ፍፃሜው ድረስ በሚያደርገው ጉዞ ምን ያስመለክታል የሚለው ይጠበቃል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!