ብልሹ አሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚስተዋልባቸው ተቋማት ላይ ስር ነቀል ለውጥ እናመጣለን- ኢ/ር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ብልሹ አሰራር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚስተዋልባቸው ተቋማት ላይ ስር ነቀል ለውጥ እናመጣለን” አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ።
ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ በአዲስ አበባ ከተማ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ከክፍለ ከተማ ዳይሬክተሮችና እና ቡድን መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
የከተማ አስተዳደሩ ለሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች የሲቪል ሰርቪስ መዋቅሩ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ኢንጂነር ታከለ ኡማ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ አላማ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የጀመረውን ስራ ከግብ በማድረስ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
በመሬት፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት ለሰራተኞች እና ለተገልጋዮች ምቹ የስራ ቦታን መፍጠር በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ዘርፎች ናቸው ብለዋል።
ህብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ሰራተኞች በክህሎት እና እውቀት ላይ ተመስርተው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ኢንጂነር ታከለ አሳስበዋል።
የመንግሥት ሰራተኛው የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ ቀልጣፋ እና ግልጸኝነት የተሞላ አገልግሎት ለህብረተሰቡ እንዲሰጥ እና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማሻሻል የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚጠቁሙ ተከታታይ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎች እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።