Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 65 በመቶ ማሳደግ ተችሏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 65 በመቶ ማሳደግ ተችሏል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ በበጀት ዓመቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን በሴክተር፣ በንዑስ ሴክተር እና በፋብሪካ ደረጃ በመለየት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በንቅናቄው በተለያዩ ምክንያቶች ከአቅማቸው በታች ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎችን በማሻሻል ከነበረበት 47 በመቶ ባለፈው ዓመት ወደ 59 በመቶ ማድረሱን እና ዘንድሮ ደግሞ ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የኃይል ፍላጎት 40 በመቶ እንደጨመረ ገልጸው÷ የኃይል ፍላጎትም አምርቶ በማቅረብ ትልቅ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

በአብዛኛው ከውጪ የሚገባውን የመስታወት ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት 600 ሺህ ቶን የሚያመርት ፋብሪካ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ትላልቅ አቅም ያላቸውን ኢንቨስተሮች በማምጣት ኢንዱስትሪውን ለማንቃት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሶላር ፓነል የሚያመርት ፋብሪካ በዚህ ዓመት መጨረሻ እንደሚመረቅም አመላክተዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.