በትግራይ ምድር አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትግራይ ክልል ወደ ግጭት እንዳይገባ አሁኑኑ ስራ እንዲጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡
በክልሉ ግጭት የሚጀመር ከሆነ ከዚህ በፊት ከምናውቀውም በላይ የከፋ በመሆኑ አስቀድሞ ማስቆም ያስፈልጋል ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፥ በትግራይ ምድር አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም ብለዋል፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት የትግራይ ህዝብ ልጆቹን ከማጣት የታደገና እፎይታን ያመጣ ስምምነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት እያሸነፈ ሰላም ይበልጣል ብሎ ውጊያ በማቆም ሲዋጉት ለነበሩ ኃይሎች መንግስት መስጠት እንደሚቻል ለእኛም ለሌሎችም ሀገራት ልምድ የሚሆን አዲስ ባህል ፈጥሯል፡፡
በክልሉ ተቋርጠው የነበሩ ትምህርት፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲሁም ፋብሪካዎች ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን አንስተዋል፡፡
መንግስት ከፈረሰ በኋላ መልሶ ማደራጀት ብዙ ፈተና እንዳለው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዛ ውስጥ ታልፎ በክልሉ መንግስት መቋቋሙን ነው ያስረዱት፡፡
በክልሉ ተፈናቅለው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ከራያ እና ጸለምት ሙሉ በሙሉ መመለሳቸውን ጠቅሰው እነዚህ ሁሉ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተገኙ ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ከወልቃይት የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግስት የጸና አቋም አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም በሁሉም ወገን ያሉ ወገኖች ተባባሪ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የታጠቁ ኃይሎችን በመንግስት በጀት ለረዥም ጊዜ ማቆየት ልማትንም ክልሉንም የሚጎዳ መሆኑን በማንሳት፥ ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ስራ መፈጸም አለበት ብለዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ በጦርነት ምንም ትርፍ እንደሌለው በማየቱ በፍጹም ጦርነት አይፈልግም፥ የመንግስትም ፍላጎት ሰላም ነው ብለዋል፡፡
መንግስት በሸኔ እና በፋኖ ተወጥሯል፥ ሰራዊቱ ስለተበታተነበት ጊዜው አሁን ነው የሚሉ አንዳንድ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ይህ ታሪክን ወደ ኋላ ተመልሶ ካለማየት የመጣ አመለካከት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የሚያግዙን ሀገራት አሉ ብለው የሚያስቡ ኃይሎችን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፥ እነዚያ ሀገራት እንኳን ሌሎችን ራሳቸውንም ማገዝ አይችሉም ብለዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ