ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን፤ ካልሆነ ግን ራሳችን እንከላከላለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን፤ ካልሆነ ግን ራሳችን እንከላከላለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ውጊያ አንፈልግም፣ ውጊያን አንመርጥም፣ ትብብርና በጋራ ማደግን ነው የምንፈልገው ብለዋል፡፡
ከሁሉም ወንድሞቻችን ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በሰላም የማያኖር ጉዳይ ካለም ራሳችን እንከላከላለን ብለዋል፡፡
ለዚህም በኢትዮጵያ ወገን የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ውጭ ህልውና የላትም፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ጎረቤቶቻችንም ህልውና የላቸውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ያልተፈቱ ችግሮች ስለነበሩ በዚያ ምክንያት ወጣ ገባ የሚሉ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚ፣ የሕዝብ ቁጥር፣ የዘመነ ሰራዊት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው÷ ከኤርትራ ጋር የጦርነት ስጋት ለሚያነሱ አካላት በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ውጊያ እንደማንፈልግ ማወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ኢትዮጵያ ትጸናለች፤ ለማጽናት የሚያበቃ በቂ አቅም አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ በታሪክ ጠላቶች ነበሯት፤ አሏት፤ አይናቸው እያየ ግን እናንሰራራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በመላኩ ገድፍ