Fana: At a Speed of Life!

የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተደራሽነት ለማስፋት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰባተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ ግልፅነትና ተደራሽነት ለማስፋት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተከናወነ ነው አለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ።

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት የሪፎርም ሥራቸውን አስመልክቶ የጋራ የውይይት መድረክ እያካሄዱ ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ቦርዱ በሕዝብና በመንግስት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የነበሩበትን የአሰራር ክፍተቶች ለይቶ ለመፍትሄው ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ካለፉት ምርጫ ሒደቶች የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመውሰድና ችግሮችን በመለየት ለቀጣዩ ምርጫ የበለጠ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ያብራሩት።

የሰባተኛውን ዙር ምርጫ ነፃ፣ገለልተኛና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመተግበር ዝግጅት እያደረገን ነው ብለዋል።

በዚህም የምርጫ ሒደቱን ፈጣንና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ የሞባይል መተግበሪያ በማበልፀግ የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ ለማከናወን ስራዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት።

የዕጩዎችና የመራጮችን ምዝገባ ለማካሄድ የሚያግዘው ቴክኖሎጂ አስተማማኝና በቦርዱ ባለሙያዎች የበለፀገ ሲስተም መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ዋና ዕምባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ በበኩላቸው÷ ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት 11ወራት ከ2 ሺህ በላይ አቤቱታዎችን መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ እንደሰጠ መናገራቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ÷ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የሚደርሱ ጥሰቶችን ማረም የሚያስችሉ ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

በተለይም አቤቱታዎች ሲቀርቡ በሁለቱም ወገን ያለውን እውነታ በማጣራት ፍትሃዊና ትክክለኛ ሪፖርት እንዲወጣና ጥሰቱ እንዲታረም እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.