”የሰቆጣ ቃል ኪዳን የማሕበረሰቡን ጤና በማሻሻል የጤና ዋስትና እየሰጠ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ የማሕበረሰቡን ጤና በማሻሻል የጤና ዋስትና እየሰጠ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እና የሰቆጣ ቃልኪዳን የ2017 ዓ.ም አፈጻጸም እና የቀጣይ ዓመት ግምገማ ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ ወቅት÷ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂና የሰቆጣ ቃል ኪዳን የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት በሀገር በቀል መፍትሔዎች ለመፍታት ለሚደረገው ርብርብ ተግባራዊ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በሰቆጣ ቃል ኪዳን የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ ላይ በተቀመጠው መሰረት የተጠቃሚዎችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ የትግበራ ወረዳዎችን የማስፋት ሥራ እየተከናነወ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ በ1 ሺህ 195 ወረዳዎች ተተግብሮ 13 ነጥብ 67 ሚሊየን በላይ እማዎራዎች እና አባወራዎች አባል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ከ63 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በ2018 በጀት ዓመትም በክልሎች መካከል የሚታየውን የአፈጻጸም ልዩነት በማጥበብ አባል መሆን የሚጠበቅባቸው ዜጎች በሙሉ አባል እንዲሆኑ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
በ2018 ዓ.ም የማስፋፋት ምዕራፍ የትግበራው ማጠቃለያ መሆኑን ጠቁመው ÷ በ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታው መሰረት ወደ ቀጣዩ የ5 ዓመታት የማስፋት ምዕራፍ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ትግበራን ለማካሔድ ቁልፍ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው÷ የሰቆጣ ቃል ኪዳን የ15 ዓመታት ስትራቴጂ ትግበራ በ334 ወረዳዎች ላይ ሲከናወን መቆየቱን አብራርተዋል በ2017 በጀት ዓመትም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ እናቶችን እንዲሁም ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሕጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራቱን ነው የተናገሩት፡፡
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ተፅዕኖን ለማሳደግ በ2018 ዓ.ም በሁለተኛ ምዕራፍ የማስፋፊያ ትግብራውን ወደ 520 ወረዳዎች ለማስፋፋት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
መቀንጨርን ዜሮ ለማድረስ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ተግባራትን ሽፋን ከፍ በማድረግና ለ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታው ሃብት በመመደብ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተመሳሳይ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።
የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ጽዱ ኢትዮጵያና ሌሎች ኢኒሼቲቮች በ2022 የተቀመጡ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የሥርዓተ ፋይናንስን ቀጣይነት ለማረጋገጥ 15 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የአባላት መዋጮ መሰብሰቡን ጠቁመው÷ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሳደግም የትኩረት መስኮችን መለየት ይገባል ብለዋል።
በለይኩን ዓለም
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡