Fana: At a Speed of Life!

በማንኩሳ ከተማ የሰላም ጥሪ የሚያቀርብ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ማንኩሳ ከተማ የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም እንዲጠናከር የሚጠይቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።

በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ በውይይት እንጅ በአፈሙዝ የሚመለስ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የለውም፤ በላቀ የህዝብ ተሳትፎ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንፈታለን ሲሉ ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ለሰላም ብለን እንጂ የደረሰብንን ዘረፋ እና ጭፍጨፋ አንረሳውም፣ ለክልላችን የሚያስፈልገው ጦርነት ሳይሆን ሰላም እና ልማት ነው እንዲሁም ሰላም የጋራ ሀብት ነው፤ በጋራ ይለማል፣ በጋራ ይጠበቃል የሚሉ መልዕክቶችን አሰምተዋል።

ለክልሉ የሚያስፈልገው ሰላም እና ልማት እንደሆነ አጽንኦት የሰጡት ሰልፈኞቹ፤ ሰላምን ለማጽናት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሀሙስ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የአማራ ክልል ህዝብ ለሰላም ያለውን ፍላጎት በሰልፍ ወጥቶ መግለጹን ማደነቃቸው ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.