የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎንደር እና በደሴ ከተሞች ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ በጎንደር እና በደሴ ከተሞች ተጀምሯል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፤ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በበጋ በመደበኛ የመንግስት የሥራ እንቅስቃሴ መከወን ያልተቻሉ ተግባራት ይፈጸማሉ።
የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ማሩ ሙሃመድ፤ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ170 ሺህ በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ 200 ሚሊየን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
በተያያዘ በደሴ ከተማ አስተዳደር የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የአረጋውያን ቤት እድሳት እና ጥገና፣ ደም ልገሳን ጨምሮ ሌሎች በጎ ተግባራት እንደሚከወኑ ጠቁመዋል።
የአስተዳደሩ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ሰይድ አራጋው እንዳሉት፤ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ114 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው 17 ዓይነት አገልግሎቶች ይሰጣሉ።
በእሸቱ ወ/ሚካኤል እና በበላይነህ ዘለዓለም