Fana: At a Speed of Life!

ህልማችን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን የሚገነባ ትውልድ መፍጠር ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አካታች የስራ እድል ፈጠራን በማሳደግ ህልማችን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን የሚገነባ ትውልድ መፍጠር ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

3ኛው የአፍሪካ የሥራ እድል ፈጠራ ፎረም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፎረሙ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ አፍሪካ የወጣቶች ምድር ናት፥ ወጣቶቻችን ሸክም ሳይሆኑ የነገ የአህጉሪቱ ተስፋዎችና አቅሞቻችን ናቸው፥ የእኛን ተጨባጭ ተግባርም ይጠብቃሉ ብለዋል።

ይህ ፎረም ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለክህሎትና ለአንድነት ወደሚሆን ንቅናቄ እንዲቀየር፣ አጀንዳው የሁሉም እንዲሆንና ወደ ዓለም አቀፋዊነት እንዲያድግ ከራዕይ የተሻገረ የተግባር ሥራ በመከወን ለወጣቶቻችን የሚመጥናቸውን ነገ እንፍጠር ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የ10 ዓመት የሀገር በቀል ሪፎርም አጀንዳችን መፈክር ብቻ አይደለም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የእድገት፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ማንም ወደኋላ የማይቀርበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢኮኖሚ መዋቅራችንን ውስጣዊ ሪፎርም በማድረግ እየቀየርን፥ በሰው ሃብት ላይ ኢንቨስት እያደረግን ነጋችንን እየገነባን ነው ብለዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል የማይበገር ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፥ አርሶ አደሩ አሁንም የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት በመሆኑ ግብርናችንን እያዘመንን እንገኛለን ነው ያሉት።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መልክዓ ምድራችንን ብቻ ሳይሆን የሰውን ሕይወት እየቀየረ ነው ያሉም ሲሆን፥ ህዝቡ ተባብሮ የተከለው 30 ቢሊዮን ችግኝ ከደን ልማት ባሻገር የስራ እድል የፈጠረና ሀገራዊ ክብር የሚገለጥበት እንደሆነ አስረድተዋል።

በችግኝ ልማት፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንዲሁም በዘላቂ አረንጓዴ የሥራ እድል ፈጠራ ሴቶችና ወጣቶቻችን የመሪነትን ሚና እየወሰዱ ነው ብለዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አርሶ አደሮችን ከገበያ ጋር በማገናኘት ሀሳብ ላላቸው የስራ እድሎችንና የእሴት ትስስር ሰንሰለት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ግብርናን በማዘመን ኢኮኖሚው በፍጥነት እንዲያድግና የበለጠ አካታች እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ሥራዎቻችንን ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ጋር በማናበብ የሚገኘውን ውጤት ለማሳደግ እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ንግድ ማለት የስራ እድል ፈጠራ፣ ስራ ማለት ክብር፣ ክብር ደግሞ ሰላም መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በለይኩን ዓለም

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.