Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የህጻናት መጫወቻዎችን መርቀው አገልግሎት አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለሚ ኩራ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የህጻናት መጫወቻዎችን መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያና የህጻናት መጫወቻ ማዕከላቱ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መሪ ሎቄ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንዲሁም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በተለምዶ መላጣ ሜዳ አካባቢ የተገነቡ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውን የቀዳማይ ልጅነት የህጻናት ማቆያና ክብካቤ ማዕከል መርቀዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በ2017 በጀት ዓመት በአጠቃላይ በመዲናዋ 15ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 122 የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲሁም 1155 የህጻናት መጫወቻዎች መሆናቸውን ገልጸው፥ በአጠቃላይ 5 ቢሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ተናግረዋል፡፡

የወጣቶች የረዥም ጊዜ ጥያቄ የሆነውን የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር ለመቅረፍ በመዲናዋ ባለፉት 3 ዓመታት ከ1ሺህ 530 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ ባለፉት 2 ዓመታት ከ3ሺህ 800 በላይ የህጻናት መጫወቻዎች መገንባታቸውን ጠቅሰው፥ በመዲናዋ እየተገነቡ የሚገኙት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ህጻናትና ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለህዝቡ የገባነውን ቃል በተግባር እየፈጸምን ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ ከመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፥ የተመረቁት ፕሮጀክቶች የእናንተ ንብረት በመሆናቸው አካባቢያችሁን ጽዱ በማድረግ ጠብቋቸው ሲሉ ለየአካባቢው ማህበረሰብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.